ወዳጆች በዚች ዓለም ላይ ሁላችንም ቦታ አለን፡፡ ዋናው ነገር ቦታውን የመለየት ብልህነቱና አስተዋይነቱ ነው፡፡ የሠው ልጅ በዚች ዓለም ላይ ሲኖር በዓለም ላይ ስሙን በክፉ አልያም በደግ ተክሎ የማለፍ ብቃት አለው፡፡ በታሪክ በክፋታቸው የተመዘገቡ ሠዎችም ቢሆኑ ለመጪው ትውልድ የሚሠጡት ትምህርት፣ ለሌሎች የሚያስቀስሙት ቁምነገር አላቸው፡፡ የጎልያድ ማአለብኝነት በትንሽ ጠጠር እንደሚተነፍስ ታሪኩ ቁምነገር ያስጨብጠናል፡፡ ትልቅ የሚመስል ትንሽ፤ ትንሽ የሚመስልም ትልቅ የሚሆንበት ዓለም ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ጎልያድም ሆነ ዳዊት እንደየባህሪያቸውና ስራቸው የሚሠጡን ትምህርት አላቸው፡፡ ቦታቸው የተለያየ ቢሆንም እኛ ከቦታቸው ትምህርት እንቀስማለን፡፡ የእዮብ ትዕግስት ፈታኝ ቢሆንም እንኳን በመጨረሻ የተጎናፀፈው ደስታ ግን ለሁላችንም አስተማሪ ነው፡፡ ትዕግስት መጨረሻዋ የደስታ ፍሬ እንደሆነ ያሳያልና፡፡ የፈርኦን ትዕቢትም ምን ያህል ዋጋ በሕይወቱ እንዳስከፈለው የሚያስጨብጠን ዕውቀት አለው፡፡ ትዕቢተኞችን ትዕቢታቸው እንደሚጥላቸው ሲያስተምረን፤ ቅኖችን ደግም ቅንነታቸው ከፍ እንደምታደርጋቸው እንደየስራ ቦታቸውና እንደታሪክ አቀማመጣቸው እንማራለን፡፡ ጃን ፖል ሳርተር የተባለው የህላዌነት (Existentialism) ፍልስፍና አራማጅ ሲናገር እንዲህ ይላል፡- ‹‹በሕይወት መገኘት የሚሠጠው ተፈጥሮ ነው፡፡ ለምሣሌ ተራራ ለምንነቱ ተፈጥሮ ከሠጠው ትርጉም ውጪ ምንም አዲስ ነገር ሊፈጥር አይችልም፡፡ ተራራ ሁሌም ተራራ ብቻ ነው፡፡ ሠው ግን ተፈጥሮ ሠውነትን ብቻ ሲሠጠው እሱ ግን በተጨማሪም ለራሱ ምንነት ትርጉም ይሠጣል፡፡ ወታደር ወይ ቄስ፤ ወይ አስተማሪ ይሆናል፡፡ ተፈጥሮ አንዴ ይፈጥረዋል፡፡ እሱ ደግሞ ራሱን በራሱ ይፈጥራል፡፡››
እውነት ነው! አምላክ ሠውን ፈጠረ፡፡ ሠው ደግሞ አስተሳሰቡን መልሶ ፈጠረ፡፡ በአስተሳሰቡም የእጁን ፍሬ በደግም ይሁን በክፉ ለራሱም ይበላል፤ ለሌላውም ያጎርሳል፡፡ ሠው ከሌሎች ተፈጥሯዊ ነገሮች የሚለየው ትልቁ ጉዳይም በሃሳቡ ራሱን መልሶ መላልሶ መስራት መቻሉ ነው፡፡ የሠው ልጅ በዚህ ድንቅ ተፈጥሮው ዓለም ላይ ጥሎ የሚያልፈው ሠናይም ሆነ እኩይ ስራ አለው፡፡ ይሄ ስራው በራሱ ላይ የሚፈጥረው ውጤት እንዳለ ሆኖ ዓለም ላይም ቦታ ይዞ ለመጪው ትውልድ ትምህርት ይሠጣል፡፡ ክፉን በክፉነቱ፣ መልካምን በመልካምነቱ ተምሮ ከክፉው የሚሸሽና መልካሙን አጥብቆ የሚይዝ ተማሪ ግን እሱ ብልሁ ተማሪ ነው፡፡
ሁላችንም በዚች ዓለም ላይ ቦታ አለን፡፡ ቦታችንን የምንወስነው ግን እኛው ራሳችን ነን፡፡ ቦታውን አሠላስሎ፣ ክፉን ደጉን ለይቶ የመወሠን ሰልጣኑንና የማገናዘብ አቅሙን ተፈጥሮ ቸሮናል፡፡ እርግጥ ነው የሠው ልጅ በአስራአንደኛው ሠዓትም ቢሆን የነበረበትን ቦታ የመለወጥም ታላቅ ችሎታ አለው፡፡ አንዳንዱ ከነበረበት ከፍታ ራሱን ዘቅዝቆ ይጥላል፡፡ ብልሁ ደግሞ ከቁልቁል ቦታው ተነስቶ ከፍታው ላይ ጉብ ይላል፡፡ ሠው ይሄን ችሎታውን ለበጎ የመጠቀም ፋንታውም፣ ምርጫውም፣ ውሳኔውም እጁ ላይ ነው ያለው፡፡ በዚህ ምርጫውም የራሱን ቦታ ይይዛል፡ ጆርጅ በርናንድ ሾው ይሄን ሃሳብ ሲያጠናክር እንዲህ ይለናል፡-‹ቀና አመለካከት ያላቸውም፣ ጨለምተኛ አመለካከት ያላቸውም፤ ሁለቱም ሠዎች ለሕብረተሰባችን አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ ቀና አመለካከት ያላቸው አይሮፕላን ሲፈጥሩ፤ ጨለምተኞቹ ደግሞ ፓራሹት ፈልስፈዋል፡፡›› ማለት በማለት ሁለቱም ጥጎች የራሳቸው ትሩፋት እንዳላቸው ይገልጻል፡፡ ወዳጆች በአጠቃላይ ቦታ የሌለው ማንም የለምና ቦታችንን ለበጎ ዓላማና ለመልካም ስራ እንለይ የዛሬው መልዕክት ነው፡፡ የት ነው ቦታችን?? ከቅኖች ረድፍ ወይስ ከጨለምተኞች ጥግ?? መልሱን ለራሳችን!
ቸር ጊዜ!
__________