ምርኮ ልብ አንጠልጣይና ተከታታይ ትረካ

ክፍል ሁለት

……ያለ የሌለ ሐይሌን አማጥጬ ቢጫው ታፔላ ላይ ለማተኮር ሞከርኩኝ።ፁሁፉ በጥቁር ቀለም የሰፈረ ሲሆን እንዲ ይላል “እንኳን ወደ ከተማችን በሰላም መጡ! የ ገሊላ ከተማ አስተዳደር” የሚል ፁሁፍ በአማርኛ ተፅፎ አየሁ። ማማተብ ፈለኩ ግራ ገባኝ እንዴት ልመጣ ቻልኩ አልኩኝ በአእምሮዬ።የታሰርኩበት ጋሪ መሄዱን ቀጥሏል ወደ ግቢው መግባት ጀመረ ልክ ያንን ሰማያዊ ያረጀ በር እንዳለፍን አካባቢው በሙሉ መቀያየር ጀመረ አይኔን ማመን አቃተኝ ያ ቢጫ ታፔላ ካይኔ ጠፋ ቀስ በቀስ ሁሉም ጠፋ በምትኩም አረንጓዴ ጫካ ይታየኝ ጀመር።

አይምሮዬ የፈጠረው ስዕል መሆኑን በማመን አይኔን ጨፍኜ ገለጥኩ ምንም የተቀየረ ነገር የለም አረንጓዴ ጫካ እና የግቢው አጥር ብቻ ነው የሚታየኝ።አጥሩም ወደ አጫጭር በመስመር ወደተተከሉ የሚያማምሩ የእንጨት አጥሮች ተቀይሯል በሩም ወደ ጥቁር የብረት ፍርግርግ ተቀይሮ አየሁ።ህልም መሰለኝ።

ያለሁበት ጋሪ ግቢው ውስጥ ቀስ ብሎ መዞር ጀመረ።ለፎቁ ጀርባውን ሰቶ ሲቆም የኔ ፊት ወደፎቁ ሆነ። ያ ያረጀ የእንጨት ፎቅ በቦታው ላይ አልነበረም በምትኩ ሰማይ ጠቀስ አረንጓዴ ህንፃ አየሁ።የማየውን ሙሉለሙሉ መቀበል አቃተኝ።በግራ መጋባትና በህመም ስሜት ውስጥ እያለሁ ድንገት ሰማያዊ የህክምና ልብስ የለበሱ በርካታ ሰዎች እኔ ወዳለሁበት ጋሪ ሲሮጡ ተመለከትኩ።

ምን እያየሁ እንደሆነ አልገባኝም።”ዶ/ር ዳንኤል” ይላሉ እየደጋገሙ።ማንን እንደሚጠሩ አልገባኝም ነበር ነገር ግን ሲቀርቡ እኔን እያዩ ስለነበር የሚጣሩት እኔን እንደሆነ ገመትኩ ግን ስሜ ዳንኤል አይደለም ደሞ የምን ዶክተር ነው? በፍጥነት የታሰርኩበትን ነገር መፍታት ጀመሩ ሲፈቱት ቀበቶ በሚመስሉ ነገሮች እንደታሰርኩ ገባኝ። ከጋሪዉ ላይ ማንሳት ሲጀምሩ ህመሙን መቋቋም ተሳነኝ ተዝለፈለፍኩኝ እንባዬ መውረድ ጀመረ
አሁንም አሁንም “ቀስ በሉ ቀስ በሉ”ይላሉ “ዳንኤል ደርሰንልሃል” አለኝ አንድ ድምፅ ድምፃቸው እየራቀኝ መጣ ሁሉም ነገር ሲጨልምብኝ ታወቀኝ እስትንፋሴ ቁርጥ ቁርጥ ማለቱን አቁሞ ጭራሽ ጠፋ….. ጠ…..ፋ…..

“ዶክተር ዳንኤል! ዶክተር ዳንኤል!” አለኝ አንድ ሰው አይኖቼ ላይ መብራት እያበራ።
“ምንድነው የምቀባጥረው ሰውዬ” አልኩት አይኔ ላይ የደገነውን መብራት በእጄ እየገፉሁት። እጄ ላይ የጉልኮስ ገመድ መሰካቱን አስተዋልኩኝ።
“ነቃህ ዶክተር? ተጨንቀን ነበር” አለኝ ሰውየው።መልኩን አየሁት በሂወቴ አይቼው አላውቅም።
“የት ነው ያለሁት?” አልኩኝ ዙርያዬን እያየዉ።ሰውየው ግራ ተጋብቶ ያየኛል።
“መልስልኝ እንጂ አንተ ማነክ?”አልኩት።ዝም ብሎ በጥርጣሬ ሲያየኝ ቆይቶ በሩን ከፍቶ ወጣ።ከአልጋው ላይ ለመነሳት ሞከርኩ።ቻልኩኝ።

ከደቂቃዎች በፊት ሲሰማኝ የነበረው ህመም አሁን የለም።ግራ ተጋባው።ጉልኮሱን ከእጄ ላይ ነቀልኩት ገመዱን ተከትዬ ወደ ጉልኮሱ ሳይ በጉልኮሱ ከረጢት ውስጥ ያለው ደማቅ ሰማያዊ ፈሳሽ ነው።”ምንድነው ይሄ?” አልኩኝ ለራሴ።ሰውየውን ለመከተል አስቤ ነበርና የተነሳሁት አልጋውን ትቼ ወደ በሩ አመራው።በመሀል አንድ የቁም መስታወት አለፍኩኝ እና የበሩን እጀታ ያዝኩኝ።ነገር ግን አንድ ነገር ቀጥ አርጎ አቆመኝ።ክው አልኩ።የበሩን እጀታ ለቅቄ ወደኃላ ተራመድኩ።መስታወቱ ፊት ደረስኩ።መስታወቱ ውስጥ ፍፁም የማላውቀውን ሰው አየው።እጅግ በጣም ደነገጥኩ።ፊቴን በእጄ ነካሁት በመዳፌ የጎልማሳ ሰው ፊት ዳሰስኩ ችምችም ያለ ጢም አለፍኩ የጎፈረ ፀጉር ነካው አማተብኩ።አይኔን ጨፈንኩ አይኔን ገለጥኩ።

የተቀየረ ነገር የለም።መስታወቱ ውስጥ ያለው ሰው ያስፈራል።የማየው ሰው ሄኖክ መሆኑን አምኜ መቀበል አቃተኝ።እኔ የ19 አመት ልጅ እንዴት የ40 አመት ሰው ልሆን ቻልኩ? ይሄ ነገር ምንድነው? በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ…አማተብኩ።ሰውየውም አብሮኝ አማተበ።ያበድኩኝ መሰለኝ።

ይቀጥላል…….ልለወዳጅዎ ሼር ያድርጉት ክፍል አንድን ከላይ ይከታተሉ

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*