ከረፈደ በእዉነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ክፍል 1

እነሆ አዲስ አጭር ልቦለድ ይዤላችሁዋለው መልካም ንባብ እንደምትወዱት ተስፋ እናደርጋለን

ያለ እረፍት የሚጮኸዉ የስልኬ ጥሪ ከተኛሁበት አነቃኝ ማልዶ የመነሳት ልምድ ስለሌለኝ የስልኬ ጥሪ አልያም ደግሞ አከራዬ ወይዘሮ ሙሉ ቤት የሚከፈተዉ መዝሙር ይቀሰቅሰኛል። እንደምንም ስልኬን አንስቼ <<ሄሎ>> አልኩኝ ሔርሜላ ነበረች
<<እንኳን ለአዲሱ አመት በሰላም አደረሰህ ቀደምኩኩ>>


አለችኝ! ድምጿ የተለየ መስህብ ነበረዉ! ሁልጊዜም ድምጿን ስሰማ የማላዉቀዉ የተስፋ ክምር በልቤ ላይ ይፈጠራል። <<እንኳን አብሮ አደረሰን የእኔ ቆንጆ>> አልኳት ከእንቅልፌ ለመላቀቅ እየታገልኩ። መስከረም 1 2008 ዓ/ም የአዲሱ አመት የመጀመሪያዋ ቀን እጅግ በማፈቅራትና በማከብራት ሴት የመልካም ምኞት ብስራት ሀ ተብሎ ተጀመረ። ከ አንድ ሰዓት በሗላ እንደምትመጣና ተነስቼ እንድጠብቃት ቀጭን ትእዛዝ አስተላልፋልኝ ስልኩን ዘጋችዉ። የወፎች ድምፅ ይሰማኛል ብሩህ ሰማያዊ ሰማይ ለስለስ ብሎ ሙዚቃዊ ስልቱን ጠብቆ ዛፎቹን ከግራ ወደ ቀኝ ከሚያስደንስ የጠዋት ንፋስ ጋር ለወራት ደምቃ ለመዉጣት ደመና ከጋረዳትና በቅርቡ ከደመና እስር ተላቃ ፍንጥቅ ብላ ከወጣች ፀሀይ ጋር ተዳምረዉ የአዲሱን ዓመት የመጀመሪያዋን ቀን ፀአዳ አልብሰዋታል…በአንድ የግል መስሪያ ቤት ዉስጥ በሾፌርነት በወር 3500 ብር እየተከፈለኝ እሰራለሁ። የመስሪያ ቤቱን ሀላፊ አቶ እንዳለን ከቦታ ወደ ቦታ ማንቀሳቀስ ስለሆነ አብዛኛዉን ግዜ ስራ አይበዛብኝም መኪናዉም እኔ ጋር እንዲያድር ፈቃድ ተሰጥቶኛል። የመኪናዉ የሰርቪስ ቀን አልፎ ፍሬን ለመያዝ ያስቸግር ነበር ከዛሬ ነገ ሰርቪስ ይደረጋል እየተባለ ቀናቶች ሳምንቶች አልፈዉ የመኪናዉን ህመም ለማከም ችላ እንደተባለ አንድ ቀን ጠዋት አቶ እንዳለ ደዉለዉ በጠዋት ቢሮ መግባት እንዳለባቸዉና እቤት ድረስ መጥቼ እንድወስዳቸዉ ትዕዛዝ ሰጡኝ። <<ሰዉ ለሰዉ መልካም ለመሆን የግድ በስጋ መዛመድ የለበትም>> የሚል አመለካከት ስላላቸዉ በመስሪያ ቤት ዉስጥ እንደ ሀላፊ ሳይሆን ሁሉም እንደ ወላጅ አባት ይቆጥራቸዋል። ወደ አቶ እንዳለ ቤት የሚወስደዉን ዋናዉን አሰፋልት ጨርሼ ወደ ቤታቸዉ የሚወስደዉን ቁልቁለታማ መንገድ ተያይዤዋለሁ ድንገት ከአንድ መታጠፊያ ዉብ የሆነች ጠይም ሴት እየሮጠች ከመኪናዉ ፊት ለፊት ድቅን አለች የመኪናዉን ፍሬን ለመያዝ ብሞክር መኪናዉ ሊቆም አልቻለም!! ህይወት እንዲህ ያሉ ክፉ ገጠመኞችን ለምን በማለዳ እንደምትሰጥ የማይፈታ እንቆቅልሽ ነዉ ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንጋጤ ጋር ፊት ለፊት ተፋጠጥኩ….

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*