2012 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ምደባ ይፋ ሆነ አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመግቢያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች በሙሉ የዩኒቨርሲቲ ምደባ በመጠናቀቁ ከዛሬ ጀምሮ መመልከት እንደሚችሉ ተገለፀ፡፡ በዚህ መሰረት ተማሪዎች በሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጄንሲ ዌብ ሳይት www.neaea.gov.et በመግባት ማየት እንደሚችሉ ነው የተነገረው፡፡ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የ2012 የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ነጥብን ጳጉሜን 6 ቀን 2011 ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ በዘንድሮው ዓመት በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ቅበላ የሚያገኙ ተማሪዎች በተፈጥሮ ሳይንስ ወንድ 46 ሺህ 416፣ ሴት 32 ሺህ 865 በድምሩ 79 ሺህ 281 ሲሆኑ ፥ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ ወንድ 34 ሺህ 838 ሴት 28 ሺህ 702 በድምሩ 63 ሺህ 540 መሆናቸው

ተገልጿል። በዚህ መሰረትም ወደ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ከሚገቡ ተማሪዎች 55 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆኑት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ሲሆኑ፥ 44 ነጥብ 5 በመቶዎቹ ደግሞ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ናቸው። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በዘንድሮው ዓመት በአጠቃላይ ወደ መንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር 142 ሺህ 821 ነው። የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች መግቢያ አራት መሰረታዊ የትምህርት አይነቶችን ውጤት መሠረት አድርጎ እንደሚወሰን መገለጹ ይታወሳል። የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ነጥቡ የሚቆረጠው በእንግሊዝኛ፣ በሂሳብ፣ የስኮላስቲክስ አፕቲቲዩድ፣ ከተፈጥሮ ሳይንስ በፊዚክስ፣ ከማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ በጂኦግራፊ የትምህርት ዓይነቶች ነው።የዘንድሮውን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ በአራት የትምህርት ዓይነቶች ብቻ እንዲወሰን
የተደረገው የጋሸበና የተጋነነ የፈተና ውጤት በመታየቱ መሆኑን የትምህርት ሚስቴርና የክልል የትምህርት ቢሮዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ መግለጻቸው አይዘነጋም። በ2011 ዓ.ም የዩኒቨርስቲ መግቢያ (የ12ኛ ክፍል) ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡት 322 ሺህ 717 ተማሪዎች መካከል 319 ሺህ 264 የሚሆኑት ፈተናውን ወስደዋል።